Sacred Texts  Bible  World Bible  Index  Previous  Next 

Amharic Bible: 1 John

1:1 ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤

1:2 ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤

1:3 እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።

1:4 ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን።

1:5 ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።

1:6 ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤

1:7 ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።

1:8 ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።

1:9 በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።

1:10 ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።

2:1 ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

2:2 እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።

2:3 ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን።

2:4 አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።

2:5 ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን፤

2:6 በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል።

2:7 ወንድሞች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረቻችሁ አሮጌ ትእዛዝ እንጂ የምጽፍላችሁ አዲስ ትእዛዝ አይደለችም፤ አሮጌይቱ ትእዛዝ የሰማችኋት ቃል ናት።

2:8 ዳግመኛ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም ነገር በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል።

2:9 በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ።

2:10 ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤

2:11 ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና።

2:12 ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ።

2:13 አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ።

2:14 አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ።

2:15 ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።

2:17 ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።

2:18 ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።

2:19 ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ።

2:20 እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ።

2:21 እውነትን የምታውቁ ስለ ሆናችሁ፥ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም።

2:22 ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።

2:23 ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው።

2:24 እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ።

2:25 እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው።

2:26 ስለሚያስቱአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ።

2:27 እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።

2:28 አሁንም፥ ልጆች ሆይ፥ በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።

2:29 ጻድቅ እንደ ሆነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ እወቁ።

3:1 የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። ስለዚህ ምክንያት ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛን አያውቀንም።

3:2 ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን።

3:3 በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል።

3:4 ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል፥ ኃጢአትም ዓመፅ ነው።

3:5 እርሱም ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም።

3:6 በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም።

3:7 ልጆች ሆይ፥ ማንም አያስታችሁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው።

3:8 ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።

3:9 ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም።

3:10 የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።

3:11 ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት። እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል ይህች ናትና፤

3:12 ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለ ምንስ ገደለው? የገዛ ሥራው ክፉ፥ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ስለ ነበረ ነው።

3:13 ወንድሞች ሆይ፥ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ።

3:14 እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል።

3:15 ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።

3:16 እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል።

3:17 ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገው ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል?

3:18 ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ።

3:19 ልባችንም በእኛ ላይ በሚፈርድበት ሁሉ፥ ከእውነት እንደ ሆንን በዚህ እናውቃለን በፊቱም ልባችንን እናሳርፋለን፥ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል።

3:21 ወዳጆች ሆይ፥ ልባችንስ ባይፈርድብን በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን፥

3:22 ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን።

3:23 ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥ ትእዛዝንም እንደ ሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ።

3:24 ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤ በዚህም በእኛ እንዲኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን።

4:1 ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።

4:2 የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥

4:3 ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።

4:4 ልጆች ሆይ፥ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ አሸንፋችኋቸውማል፥ በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና።

4:5 እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለሙም ይሰማቸዋል።

4:6 እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን።

4:7 ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ።

4:8 ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።

4:9 በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።

4:10 ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።

4:11 ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል።

4:12 እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል።

4:13 ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን።

4:14 እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን።

4:15 ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል።

4:16 እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል።

4:17 በፍርድ ቀን ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል፤ እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና።

4:18 ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።

4:19 እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።

4:20 ማንም። እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?

4:21 እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።

5:1 ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል።

5:2 እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን።

5:3 ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።

5:4 ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው።

5:5 ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?

5:6 በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም።

5:7 መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው።

5:8 የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ።

5:9 የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና።

5:10 በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።

5:11 እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው።

5:12 ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።

5:13 የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ።

5:14 በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል።

5:15 የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን።

5:16 ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይለምን፥ ሞትም የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል። ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፤ ስለዚያ እንዲጠይቅ አልልም።

5:17 ዓመፃ ሁሉ ኃጢአት ነው፥ ሞትም የማይገባው ኃጢአት አለ።

5:18 ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንዳያደርግ፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተወለደው ራሱን እንዲጠብቅ ክፉውም እንዳይነካው እናውቃለን።

5:19 ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።

5:20 የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።

5:21 ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።


Next: 2 John