Sacred Texts  Bible  World Bible  Index  Previous  Next 

Amharic Bible: James

1:1 የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን።

1:2 ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት

1:4 ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።

1:5 ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል።

1:6 ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና።

1:7 ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው።

1:9 የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና።

1:11 ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል።

1:12 በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።

1:13 ማንም ሲፈተን። በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።

1:14 ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።

1:15 ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።

1:16 የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ።

1:17 በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።

1:18 ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን።

1:19 ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤

1:20 የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።

1:21 ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ።

1:22 ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።

1:23 ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤

1:24 ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል።

1:25 ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል።

1:26 አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው።

1:27 ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።

2:1 ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ።

2:2 የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥

2:3 የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ። አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም። አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን?

2:4 ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን?

2:5 የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን?

2:6 እናንተ ግን ድሆችን አዋረዳችሁ። ባለ ጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤትም የሚጎትቱአችሁ እነርሱ አይደሉምን?

2:7 የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን?

2:8 ነገር ግን መጽሐፍ። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ እንደሚል የንጉሥን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤

2:9 ለሰው ፊት ግን ብታደሉ ኃጢአትን ትሠራላችሁ፥ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይወቅሳችኋል።

2:10 ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ፥ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል፤ አታመንዝር ያለው ደግሞ። አትግደል ብሎአልና፤

2:11 ባታመነዝርም፥ ነገር ግን ብትገድል፥ ሕግን ተላላፊ ሆነሃል።

2:12 በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፥ እንዲህም አድርጉ።

2:13 ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና፤ ምሕረትም በፍርድ ላይ ይመካል።

2:14 ወንድሞቼ ሆይ፥ እምነት አለኝ የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን?

2:15 ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥

2:16 ከእናንተ አንዱም። በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል?

2:17 እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።

2:18 ነገር ግን አንድ ሰው። አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፥ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል።

2:19 እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል።

2:20 አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን?

2:21 አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን?

2:22 እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን?

2:23 መጽሐፍም። አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ።

2:24 ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ።

2:25 እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?

2:26 ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።

3:1 ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና።

3:2 ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው።

3:3 እነሆ፥ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፥ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን።

3:4 እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ።

3:5 እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል።

3:6 አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል።

3:7 የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፥ ደግሞ ተገርቶአል፤

3:8 ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው።

3:9 በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤

3:10 ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም።

3:11 ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን?

3:12 ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም።

3:13 ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ።

3:14 ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ።

3:15 ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤

3:16 ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና።

3:17 ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።

3:18 የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።

4:1 በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን?

4:2 ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤

4:3 ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም።

4:4 አመንዝሮች ሆይ፥ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።

4:5 ወይስ መጽሐፍ። በእኛ ዘንድ ያሳደረው መንፈስ በቅንዓት ይመኛል ያለው በከንቱ እንደ ተናገረ ይመስላችኋልን?

4:6 ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ። እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል።

4:7 እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤

4:8 ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ።

4:9 ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ።

4:10 በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።

4:11 ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም።

4:12 ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?

4:13 አሁንም። ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ፥ ተመልከቱ፥ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና።

4:14 ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና።

4:15 በዚህ ፈንታ። ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል።

4:16 አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው።

4:17 እንግዲህ በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው።

5:1 አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፥ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ።

5:2 ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፥ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል።

5:3 ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፥ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል። ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል።

5:4 እነሆ፥ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፥ የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ፀባዖት ጆሮ ገብቶአል።

5:5 በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል።

5:6 ጻድቁን ኰንናችሁታል ገድላችሁትማል፤ እናንተን አይቃወምም።

5:7 እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል።

5:8 እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።

5:9 ወንድሞች ሆይ፥ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ፥ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል።

5:10 ወንድሞች ሆይ፥ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ።

5:11 እነሆ፥ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፥ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።

5:12 ከሁሉም በፊት፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በሰማይ ቢሆን በምድርም ቢሆን በሌላ መሐላም ቢሆን በምንም አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፥ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን።

5:13 ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር።

5:14 ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት።

5:15 የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል።

5:16 እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።

5:17 ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥

5:18 ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች።

5:19 ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው፥

5:20 ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ።


Next: 1 Peter